Skip to main content
በክልሉ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ 90 ፕሮጀክቶች ግንባታ በዛሬው ዕለት በይፋ ተጀምሯል፦ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው
ሆሳዕና ታህሳስ 06/2017 ዓ.ም
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ እንዳሻው ጣሰው በተገኙበት ክልል አቀፍ የኮሪደር ልማት እና የአንድ ከተማ አንድ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር ማስጀመሪያ ፕሮግራም በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።
በዚህ ወቅት ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ እንዳሻው ጣሰው ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት፦ ከተሞቻችንን የማዘመንና የማስዋብ ለህብረተሰቡ አመቺ ማድረግ የመንግስታችንና የፓርቲያችን የፖሊስ ኘሮግራም ውጤቶች ናቸው።
የኮሪደር ልማት ስራዎች ለማከናወን ከአምስት ወራት በላይ የፈጀ የቅድመ ዝግጅት ስራ በዋናነት ከተሞችን የመለየት ዲዛይን የማውጣት በየከተሞች የሚሰሩ ቦታዎችን ማዘጋጀት የሚሸፈን ኪሎሜትር መለየት የስራ ማኑዋልና መመሪያ የማዘጋጀት እንዲሁም ከአመራርና ከህዝብ የመወያየት ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።
በዚህም በክልል ማዕከል ከተሞች በሆሳዕና ከተማ 35ኪ.ሜ በወራቤ፣በቡታጅራ፣በወልቂጤ እና በዱራሜ ከተሞች 25ኪ.ሜ በሀላባና 20ኪ.ሜ በሳጃ 10ኪ.ሜ የኮሪደር ልማት ስራ እንደሚሰራ በዝርዝር አብራርተዋል።
የኮሪደር ልማት ስራው በሁለት ምዕራፍ እንደሚሰራ የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ እስከ ሰኔ 30/2017 አጠቃላይ ስራው ተጠናቆ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
በዚህ የህብረተሰቡ ተሳትፎ የማይተካ ሚና አለው ያሉት ርዕሰ መስተዳድር በተለይ ባለሀብቶች፣የንግዱ ማህበረሰቦች፣በተለያዩ የውጪ ሀገራት የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች፣መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ባንኮች ኢንሹራንሶች ከተሞችን ለማዘመን በሚደረገው እንቅስቃሴ በመሳተፋ ሀገራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የኮሪደር ልማት የተሰራባቸው ከተሞች ለእግረኞች ምቹ የከተማን ውበት የሚቀይር የማይሰለቹ የመኖሪያ አከባቢ ከመሆን ባሻገር ገቢንም የሚያስገኙ እንደሆነ ተናግረዋል።
አዳማ ላይ በነበረው የአመራሮች የስልጠና መድረክ ማጠቃለያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባስቀመጡት የአንድ ከተማ አንድ ፕሮጀክት አቅጣጫ መሠረት በክልሉ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ 90 ፕሮጀክቶች በ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል እንደሚገነባ ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸው በክልሉ ሁሉም አካባቢ በዛሬው ዕለት በይፋ መጀመሩን አስታውቀዋል።
ህዝቡ የኮሪደር ልማትና "የአንድ ከተማ አንድ ኘሮጀክት" ስራ እንዲሳካ ቀንተሌት በመሳተፍ የስራው ባለቤት እንዲሆኑ አንዲሁም አመራሩ በመያያዝ በሙሉ አቅሙ ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስራ እንዲሰሩ በአጽንኦት ገልጸዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በበሆሳዕና ከተማ "የአንድ ከተማ አንድ ኘሮጀክት" አካል የሆነው የህዝብ መድኃኒት ቤት ግንባታ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።
የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቴዎስ አኒዮ በበኩላቸው የኮሪደር ልማት ስራ በዞኑ እስከአሁን እየተሰሩ ያሉ የልማት ስራዎችን በጉልህ የሚያሳድግ በመሆኑ ህዝቡ እስከአሁን እየሰጠ ያለውን አውንታዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
የዞኑ አስተዳደር ፕሮጀክቶችን ወደ መሬት ከማውረድ ጎን ለጎን ለሰላምና ፀጥታ፣ ለአረንጓዴ ልማትና ለሌማት ትሩፋት፣ የኑሮ ውድነትን ለማቃለል፣ ለስራ ዕድል ፈጠራ እና የመንግሥትን ገቢ በሚገባው ልክ ለመሰብሰብ በትጋት እየሰራን ነው ብለዋል።
የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዳዊት ጡንደዶ በመድረኩ 36 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ከተማዋን ውብና ማራኪ፣ ለኑሮና ለስራ ምቹ ያደረጋታል ብለዋል።
አቶ ዳዊት በከተማው በአጠቃላይ 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በጀት ተመደሸቦላቸው እየተሰሩ ያሉ ፕሮጀክቶች በበጀት አመቱ እንደሚጠናነቁ ተናግረዋል።
Image